መገናኛ ብዙኃን የዜጎችን የአብሮነት ዕሴት የሚያጠናክሩ መረጃዎችን በማድረስ የሀገርን ሰላምና ዕድገት መደገፍ ይጠበቅባቸዋል መገናኛ ብዙኃን የዜጎችን የአብሮነት ዕሴት የሚያጠናክሩ መረጃዎችን በማሰራጨት የሀገርን ሰላምና ዕድገት የመደገፍ ኃላፊነታቸውን መወጣት እንደሚጠበቅባቸው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር መሐመድ እድሪስ ተናግረዋል። የህዝብና የንግድ መገናኛ ብዙኃን የሥራ ኃላፊዎችና ተወካዮች የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣንን ተቋማዊ የሥራ እንቅስቃሴና የለውጥ እርምጃዎች ጎብኝተዋል። በጉብኝቱ የተሳታፉ የመገናኛ ብዙኃን ኃላፊዎችም የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዘርፉን ለማሳደግ ያከናወናቸው ተግባራት አበረታች መሆናቸውን ተናግረዋል። የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር መሐመድ እድሪስ፤ የመገናኛ ብዙኃን የሥራ ኃላፊዎች የተቋሙን የለውጥ እርምጃዎች እንዲገነዘቡ በማድረግ ትብብርን ማስፋት የጉብኝቱ ዓላማ ነው ብለዋል። በመገናኛ ብዙኃን ላይ የሚደረገው ህግን የተከተለ አስቻይ የቁጥጥር ስራ መረጃን የሚያሰራጭ ማንኛውም የመገናኛ ዘዴ ለሀገርና ለህዝብ ጥቅም ቅድሚያ እንዲሰጥ የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል። በባለስልጣኑ አዋጅ ቁጥር 1238/2013 ዓ.ም መገናኛ ብዙኃን ለዜጎች አብሮነትና ለሀገር ሁለንተናዊ ሰላምና ዕድገት የሚበጅ መረጃን ማድረስ ዐቢይ ጉዳይ ተደርጎ መደንገጉን ተናግረዋል። በዚህም ለህዝብ የሚደርስ ማንኛውም መረጃ ከሀሰት የጸዳ፣ ልማትን የሚደግፍ፣ የዜጎችን የአብሮነት ዕሴት የሚጠብቅ እንዲሁም ለሀገር ሰላምና ልማት ገንቢ ሚና የሚወጣ መሆን አለበት ብለዋል። ህጋዊ የአሰራር ሂደትን በማይከተሉ የመገናኛ ዘዴዎች ላይ በመማማርና በመደጋገፍ ላይ የተመሰረተ አስቻይ ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል። ከህዝብና ሀገር ጥቅም በተፃራሪ መረጃን በሚያሰራጩ የመገናኛ ዘዴዎች ላይ ህጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃ እንደሚወሰድ በአጽንኦት አስገንዝበዋል። የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ጌትነት ታደሰ፤ የባለስልጣኑ የለውጥ እርምጃ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት የመስጠት አካል ተደርጎ እንደሚታይ ገልጸዋል። ባለስልጣኑ እየተከተለ የሚገኘው በቴክኖሎጂ የተደገፈ የመረጃ መለዋወጥ፣ ማሰባሰብና ትንተና ተልዕኮውን መወጣት የሚያስችል ስራ መሆኑን ተናግረዋል። የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሙሉቀን ሰጥዬ፤ የለውጥ ስራዎቹ መገናኛ ዘዴዎችን መምራት የሚያስችል አቅም በመፍጠር ለተቋማዊ ግንባታ ልምድና ትምህርት የሚወሰድበት ነው ብለዋል። ባለስልጣኑ በመገናኛ ብዙኃን ክትትል ስራ በሚያሰባስባቸው የመረጃ ውጤቶች በተገኙ ስኬቶችና ግድፈቶች ዙሪያ መማማር እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል። የአሐዱ ራዲዮ እና ቴሌቪዥን ዋና ስራ አስኪያጅ ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ፤ ባለስልጣኑ ባለፉት ዓመታት አሰራሩን በማሻሻል እምርታዊ ለውጥ ካስመዘገቡ ተቋማት አንዱ መሆኑን ተገንዝበናል ብለዋል። በአዲስ መልክ ተግባራዊ የተደረጉ የህግ፣ የደንብና የአሰራር ማሻሻያዎችም ለመገናኛ ብዙኃን ምቹ የሥራ ምኅዳር እንዲፈጠር ማድረጋቸውን ገልጸዋል። የዓባይ ቴሌቪዥን ሥራ አስኪያጅ ግሩም ይልማ፤ ባለስልጣኑ የዘረጋቸው በቴክኖሎጂ የተደገፉ የአገልግሎት መስጫ ሥርዓቶች ለቀጣይ ስራ ትልቅ ስንቅ ናቸው ብለዋል። የመገናኛ ብዙሃን ለዜጎች የሚጠቅም መረጃን በማድረስ ለአብሮነት፣ ለሀገር ግንባታ፣ ለሰላምና ደህንነት የበኩላችንን አስተዋጽኦ ማድረግ ይጠበቅብናል ሲሉም ተናግረዋል። የባለሥልጣኑን የመገናኛ ብዙኃን የክትትል፣ ድጋፍ፣ ቁጥጥርና አስተዳደር እንዲሁም ተቋማዊ የሥራ እንቅስቃሴና የለውጥ እርምጃዎችን አስመልክቶ የባለስልጣኑ የሥራ ኃላፊዎች ገለጻ አድርገዋል። ኢዜአ
30
May
2024