በደብረ ብርሃን ከተማ በቀን 100 ሺህ ሊትር ወተት እንደሚመረት ተጠቆመ

በደብረ ብርሃን ከተማ በቀን 100 ሺህ ሊትር ወተት እንደሚመረት ተጠቆመ በደብረ ብርሃን ከተማ የሌማት ቱርፋት ፕሮግራም ከተጀመረ ወዲህ በቀን ከ60 ሺህ ወደ 100 ሺህ ሊትር ወተት በቀን ማምረት መቻሉን ተገለጸ። በደብረ ብርሃን ከተማ የተለያዩ የእንሰሳት እርባታ ስራ እየተሠራ መሆኑን የደብረ ብርሃን ከተማና የሰሜን ሸዋ ዞን በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች ተዘዋውረው ተመልክተዋል። በፕሮግራሙ ላይ የደብረ ብርሃን ከተማ ተቀዳሚ ከንቲባ አቶ በድሉ ውብሸትን ጨምሮ የክልል የከተማ ፣የዞን በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች እንዲሁም የግብርና ባለሙያዎች ተገኝተዋል። በጉብኝታቸውም ምሳሌ አግሮ ኢንዱስትሪና ቡሬ የእንሰሳት ማቀነባበሪያ ኀላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ፣ የሜሪስ የእንሰሳት ዝርያ ማሻሻያ ፕሮጀክትን እንዲሁም ዜድ ኤ ኤም ቢዝነስ የበግና የፍየል እርባታና ዘር ማሻሻያን ኃ/የተወሰነ የግል ማህበርን ከፍተኛ አመራሮቹና ባለሙያዎቹ ተዘዋውረው ተመልክተዋል። የእንሰሳት ዘርፉ በስራ እድል ፈጠራ እንዲሁም የማህረሰቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥበትን ሁኔታም አመራሮቹ ተዘዋውረው ተመልክተዋል። የደብረ ብርሃን ከተማ ተቀዳሚ ከንቲባ አቶ በድሉ ውብሸት በጉብኝታቸው እንዳነሡትም እንደከተማ የሌማት ቱርፋት ፕሮግራም ከመጀመሩ በፊት በቀን 60 ሺህ ሊትር ወተት ይመረት የነበረውን ወደ 100 ሺህ ሊትር ማሳደግ ተችሏል ብለዋል። የእንሰሳት ዝርያዎችን በማሻሻል፣ የመኖ አቅርቦት በማሳደግና በማሻሻል ስራ ተሰርቶ ለውጥ ማንጣት መቻሉንም አንስተዋል። በእለቱ የሌማት ቱርፋት ውጤቶች መጎምኘታቸውንም ገልጸዋል። ባለፉት 9 ወራት 185 ሺህ በላይ የአንድቀን ጫጩት በቀን ማስፈልፈል መቻሉንም ጠቁመዋል። በተለያዩ የእንሰሳት ዘርፎች ከዚህ የበለጠ እንደሚሰራም አመላክተው በተለይም የእንሰሳት ዘርፉ ላይ ሰፊ የስራ እድል ለመፍጠር እንደከተማ እየተሠራ መሆኑንም ጠቁመዋል። በስራ እድል በኩል በእንሳሳት ዘርፍ 50 ኢ/ዝ እና በዶሮ እርባታ 40 ኢ/ዞች እየተደራጁ እንደሚገኙም ገልጸዋል። የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መካሻ አለማየሁ አያይዘው እንዳሉትም ለእንሰሳት እርባታ ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ዘርፉ እንዲጠናከር ሰፊ ስራ ተሰርቷል ብለዋል። የጤና ኬላ ማጠናከር ፣ የሰው ሀይል አቅርቦት፣ የእንሰሳት ጤና ክትትሉ ላይ ሰፊ ድጋፍ መደረጉን ጠቅሰው የእንሰሳት ዝርያ ማሻሻያ ምርታማነትን ለማሳደግ በትኩረት እየተሠራ እንደሚገኝም አንስተዋል። በአንጎለላና ጣራ ወረዳ አርሶ አደሮችና ባለሀብቶች በዚህ በእንሰሳት ዘርፍ ተሳስረው እየሰሩ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

Share this Post